የአራት ረጂም ልብወለድ መጻህፍት ደራሲ ነች:: ከቤተሰብ ጋር ወደ ሆላንድ ሄዳ ሳለች፣ ከ1993 ዓ. ም. ጀምሮ እስከ 1994 ዓ. ም. ባለው ጊዜ የመጀመሪያ መጽሀፏን ‘’ምንዳ’’ን ጽፋ ጨረሰች:: ይህንን ሥራዋን ግን ወዲያው ለአንባቢያን አላቀረበችም:: ከሆላንድ ወደ እንግሊዝ ሀገር መጥታ፣ ዓመታት ቆይታ በ2001 ዓ. ም. ነው ያሳተመችው:: ሁለተኛ መጽሀፏን “ሕልመኛዋ እናት”ንም በ2004 ዓ. ም. ለአንባቢያን አቅርባለች:: የአዲስ አበባን ውጣ ውረድ፣ ሳቅ ሀዘን፣ የሠፈር ፈረሳ፣ ፍቅር፣ ወዘተ በአንድ ወጥ ታሪክ ህይወት ሠጥቶ የሚያቀርብልንን ሶስተኛ መጽሀፏን “ተፈናቃይ ፍቅር”ንም በ2008 ዓ. ም. ያቀረብችልን በቋሚነት ከምትኖርበት ከለንደን ከተማ ነው:: “የመሀረቡ ምስጢር“ የሚለውን አራተኛ መጽሀፏን ደግሞ በ2015 ዓ. ም. ለአንባቢያን አቅርባለች።
እታለም እሸቴ ኢትዮጵያ፣ በሰሜን ሸዋ፣ ሞላሌ፣ ሠሥ በር የተባለው ቦታ ነው የተወለደችው:: በልጅነቷ ወደአዲስ አበባ መጥታ፣ አያቷ በሚኖሩበት በአሮጌው ቄራ ከየኔታ ልሳነ ወርቅ ጋ ለጥቂት ጊዜ ፊደል ቆጥራለች:: እንደገና ወደተወለደችበት ቦታ ተመልሳ፣ ሞላሌ በሚገኘው በአቤቱ ነጋሲ ወረደቃል ትምህርት ቤት ከ 1ኛ እሰክ 3ኛ ክፍል ተምራለች:: ዳግመኛ ወደ አዲስ አበባ መጥታ፣ ፊትበር ፖሊስ ጋራዥ ጀርባ በነበረው ጥበብ መንገድ ትምህር ቤት ከ4ኛ እስከ 6ኛ ክፍል ተምራለች:: የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷዋንም በዑራኤል መለስተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ደግሞ በዳግማዊ ምኒልክ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትላለች:: ወደ ውጭ ከወጣች በሁዋላም የተለያዩ ስልጠናዎችን ወስዳለች:: ከሌላው ከሌላው የባዕድ ሀገር ህይወትና ሥራ ጋር በማጣመር ነው እነኝህን አራት ድንቅ የረጂም ልብወለድ መጽሀፍት ያቀረበችልን:: ሌሎችንም ተጨማሪ ሥራዎቿን ልታቀርብልን በመጻፍ ላይ ትገኛለች::
የሀገራችን ታዋቂ ሀያሲና ጸሀፊ አቶ አስፋው ዳምጤ እታለምን በተፈጥሮ የመተረክ ስጦታ የታደለች born narrator ይሏታል። በታዋቂ ጸሀፊ እና ገጣሚ ሀማ ቱማ አስተያየት መሠረት ደግሞ በየታሪኮቿ የምታነሳቸው ገጸባህርያት ቋንቋቸው የየራሳቸው የሆነ የተዋጣለት የቋንቋ አጠቃቀም ያላት ደራሲ ነች።